በሴቶች ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ጎጅ ባህላዊ ድረጊቶችን በመከላከል ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸዉን ለማረጋገጥ ሁሉም የድርሻዉን እንድወጣ ተጠየቀ፡፡
የዘንድሮው የሴቶች ቀን ‹‹ የሴቶችን መብት የሚያሰከብር ህብረተሰብ እንገንባ›› በሚል መሪ ሀሳብ በዓለም ለ110ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ45ኛ ጊዜ በደቡብ ወሎ ዞን ተከብሯል፡፡
በበዓሉ አከባበር የደቡብ ወሎ ዞን ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ አስታጠቅ ግዛው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አለም አቀፉ የሴቶች ቀን የሴቶችን ሁለንተናዊ ፈተናዎች በመታገል መብቶቻቸዉ እንዲከበር የሚዘከርበት ልዩ ዕለት ነዉ ብለዋል፡፡
በዚሁ ታሪካዊ ዕለት በክልል ሆነ በዞን ደረጃ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከርና አሁንም በተለያየ ደረጃ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ጨምሮ የሚደርሱባቸዉን ዘርፈ ብዙ ጫናዎችን በመከላከል ለመብቶቻቸዉ መከበር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ወ/ሮ አስታጠቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን የብልፅግና ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ መኮነን በበኩላቸው የኢትዮጵያዊያን ሴቶች በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ በማለፍ ራሳቸውን ከማብቃት አልፈው የኢትዮጵያን ስም በዓለም ያስጠሩ እንደ ጣይቱ አይነት ጀግና ሴቶች እንዳሉ ተናግረዋል።
በባለፉት ጊዚያቶች ሴቶች በብዙ ጭቆናና አፈና ዉስጥ የቆዩ ቢሆንም አሁን ግን በሀገራችን በሁሉም መስኮች ሴቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም በሀገራችን የሴቶችን የአመራር ሰጪነታቸዉን ሚና ከፍ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልፀዉ ሴቶች ራሳቸዉም በራስ የመተማመናቸዉን ብቃት በእጅጉ ማሳደግ እንዳለባቸዉ አስገንዝበዋል ፡፡
ማርች 8 የቅንጦት በዓል ሳይሆን ሁሌም ልንተገበረው የሚገባ ተግባር ነው ያሉት አቶ ኤርሚያስ ህብረተሰቡ በየዕለቱ የሴቶችን የስራ ጫናና ተሳትፏቸዉን በማሰብ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
በበዓሉ ከተሳተፉ ሴቶች መካከል ወ/ሮ ወሰን አይቸው እና ኮማንደር አባይነሽ ከበደ በሰጡት አስተያየት በማህበራዊ፤በኢኮኖሚና በፖለቲካ ዘርፍ የሴቶች ሚና ከፍተኛ ቢሆንም በሁሉም ዘርፍ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ብዙ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።
ሴቶች በተለያዩ የስራ መስኮች በከፍተኛ ኃላፊነት ተሰማርተው ቢገኙም አሁንም እድሉን ያላገኙና እራሳቸውን ደብቀው የሚገኙ ሴቶች መኖራቸው ተናግረዋል።