በቅርቡ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በደቡብ ወሎ ዞን ውጤታማ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎችን መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡
በዚህም ርዕሰ መስተዳድሩ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት በአማራ ክልል የሚገኙ የ15 ዞኖች ከፍተኛ አመራሮች በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ የሚገኘውና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መስጠት የጀመረውን የደለመኔ ተፋሰስ ልማትን በመጎብኘት ልምድ እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡
የአዊ ብሔረሰብ ዞን ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ አጅበው ስንሻው እና የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ አዲስ ተፈራ የአካባቢው ህብረተሰብ እና አመራሩ የተራቆተና የተጎሳቆለውን ተራራ አልምተው ዘርፉን ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠሪያ በማድረግ ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ መጀመራቸው አዲስ መሬት መፍጠር እንደሚቻል ተምረንበታል ብለዋል፡፡
ይህንንም ልምድ በአካባቢያቸው በመተግበር የአርሶ-አደሮችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩም ነው የጉብኝቱ ተሳታፊ ከፍተኛ አመራሮች የተናገሩት፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሀመድ በዞኑ ትልቁ ፀጋ የሆነውን የህዝቡን ጉልበት በመጠቀም እንደየ አግሮ ኢኮሎጂው የፍራፍሬ፣የእንስሳትና የሰብል ልማትን በማልማት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህም ውስጥ በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ህብረተሰቡ ጉልበቱን በመጠቀም ተራራዎችን ከነበሩበት መጎሳቆል በማውጣት የሀብት ምንጭ ከማድረጋቸውም በላይ ዘርፉን ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠሪያ የሆነውን ተፋሰስ ልማት በመጎብኘት ተራሮችን በተቀናጀ መንገድ እንዴት ማልማትና በአጭር ጊዜ የሀብት ምንጭ ማድረግ እንደሚቻል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ልምዱን በሁሉም ዞኖች ለማስፋት የታሰበ ፕሮግራም ነው ብለዋል፡፡የአርጎባን ተሞክሮን በሁሉም ወረዳዎች የማስፋት ስራ እየተሰራ መሆኑንም በመጠቆም፡፡
የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ኡመር ሁሴን ተራራማ ቦታዎችን ወደ ፍራፍሬ ልማት ለምን ማስገባት አንችልም ብለን መጀመሪያ በአመራር ደረጃ ከዚያም ህብረተሰቡ ጋር በመወያየትና በመግባባት በተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆን ችለናል ብለዋል፡፡