September 06,20 10 26,01

ተራራን በማልማት እና ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በፍቅር አብሮ በመኖር የአርጎባ ብሔረሰብ ትልቅ ምሳሌ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡

#

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በመሆን በደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

ጉብኝት ከተደረገባቸው መካከል በአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ 01 ቀበሌ የሚገኘው ደለመኔ ተፋሰስ አንዱ ነው፡፡ተፋሰሱ 200 ሄክታር ሽፋን አለው፡፡እጅግ የተራቆተና የተጎሳቆለውን ተራራ የአካባቢው አርሶ-አደሮችና ወጣቶች አልምተው ሁለት ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ፓፓያና ማንጎን ጨምሮ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን አምርተው ገበያ በማቅረብ 220 ወጣቶች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡

የኮንሶ ተፋሰስ እንደሀገር መልካም ተሞክሮ ይነሳል የአርጎባ ተፋሰስን ደግሞ ልዩ የሚያደርገው ባለተመቸ ቦታና ውሃ በሌለበት አካባቢ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታችሁን ያሳችሁበት በመሆኑ ጀግና ያሰኛችኋል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ፡፡

የተፋሰስ ልማቱ በአትክልትና ፍራፍሬ ከሚገኘው ጥቅም በተጨማሪ አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ ይቻላል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ሌሎች ከአርጎባ ብሔረሰብ የሚማሩት የተራራ ልማትን ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋር በፍቅር አብሮ የመኖር ባህልና ልምድንም ጭምር ሊሆን እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ ታደሰ ግርማ እንደተናገሩት ደግሞ በዞን ደረጃ ተራሮችን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለመቀየር አቅጣጫ በማስቀመጥ የአርጎባን ተሞክሮ 21 ወረዳዎች ልምድ እንዲወስዱ በማድረግ በሁሉም ወረዳዎች በሁለት በሁለት ተፋሰሶች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡

የአርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ኡመር ሁሴን የወረዳቸው ልማት በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በመጎብኘቱ እንዳስደሰታቸው ተናግረው ይህም ህዝቡንም ሆነ አመራሩን እና ባለሙያውን ለላቀ ስራ ያነሳሳል ብለዋል፡፡

ከተፋሰስ ልማቱ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወጣት መሀመድ ኑሩ ከአሁን በፊት ተጠቃሚ እንዳልነበሩ በመግለፅ አሁን በተፋሰሱ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማታቸውና ተጠቃሚ በመሆናቸው ሌሎች ወጣቶችንም እንዳነሳሳቸው ይናገራል፡፡

በቃሉ ወረዳ 01 ቀበሌ የሚገኘው 69 ሄክታ ሽፋን ያለው የማንጎ ክላስተር እና ደጋን አካባቢ የሚገኘው የጨለቃ መስኖ ፕሮጀክት ጉብኝት ከተደረገባቸው የልማት ስራዎች መካከል ይገኙበታል፡፡